የዲጂታል ክፍፍል
የበይነመረብ ተዳራሽነት መጓደል የኢትዮጵያ አቅም ላይ የጣለው እንቅፋት
በ2013፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ "ኢንተርኔት ውሃ ወይም አየር አይደለም" ማለታቸው ይታወሳል።
ነገር ግን የበይነመረብ አገልግሎት ለዘመናዊ ኅብረተሰቦች ኅልውና ወሳኝ ሀብት እየሆነ ነው።
ካርድ ውስጥ አስተማማኝ እና በተመጣጣኝ ዋጋ የሚቀርብ የበይነመረብ አገልግሎት የኢትዮጵያን ኢኮኖሚያዊ እና ዲሞክራሲያዊ ስርዓተ ማዕከል የመሆን አቅም ያሳድጋል ብለን እናምናለን።
ነገር ግን ከአራት ኢትዮጵያውያን መካከል አንዳቸው ብቻ የበይነመረብ ተጠቃሚ በመሆናቸው ምክንያት ገና ብዙ ይቀረናል።
የኢትዮጵያ መንግሥት፣ ብዙ ሰዎች የበይነመረብ ተጠቃሚ ቢሆኑ የሚገኘውን ጥቅም "የበይነመረብ ተዳራሽነት ለዲጂታል ትራንስፎርሜሽን መሠረት ሲሆን፣ ማኅበረ ኢኮኖሚያዊ ልማትን ያሳልጣል" በማለት ያምናል።
ይህንን የሚያጠናክር መረጃም አለ።
በአፍሪካ ውስጥ የ10 በመቶ የሞባይል ብሮድባንድ ተዳራሽነት መጨመር፣ የዜጎችን የነፍስ ወከፍ ገቢ በ2.5 በመቶ እንደሚጨምር ታይቷል። የሞባይል በይነመረብ አገልግለቶ ተደራሽነትን መጨመር እንዲሁ የመሠረተ ልማት ማዳረስ ጉዳይ ብቻ አይደለም። ተመሳሳይ ጥናት የሞባይል በይነመረብ አገልግሎት ዋጋ በ10 በመቶ ሲቀንስ የተጠቃሚዎች ቁጥርም በ3.1 በመቶ እንደሚጨምር ያሳያል።
ይህንን እስኪ በደንብ እናብራራው።
አሁን 2ጂቢ በይነመረብ 2.71 ዶላር (140 ብር ገደማ) ይፈጃል፤ አሁን ያሉት ተጠቃሚዎች ደግሞ 23,000,000 ናቸው።
ዋጋው በ10 በመቶ ቢቀንስ እና 2.44 ዶላር (126 ብር ገደማ) ቢሆን፣ የተጠቃሚዎቹ ቁጥርም በ737,800 ይጨምራል።
ነገር ግን የ2.5 በመቶ ጠቅላላ የአገር ውስጥ ገቢ ዒላማ ላይ ለመድረስ፣ ተጨማሪ 1,642,200 ተጠቃሚዎች ያስፈልጋሉ። ይህም የበይነረመረብ ዋጋው 32 በመቶ በመቀነስ 1.84 ዶላር (95 ብር ገደማ) መሆን አለበት።
ስለዚህ፣ 26,180,000 ተጠቃሚዎች ሲኖሩ፣ የ2.5% ጠቅላላ የአገር ውስጥ ገቢ ዕድገት እንጠብቃለን።
ሁሉም ተጠቃሚዎች 3.77 ዶላር (190 ብር ገደማ) ቢከፍሉ፣ ኢትዮቴሌኮም 9.2 ሚሊዮን ዶላር (478 ሚሊዮን ብር ገደማ) ገቢ ያጣል።
ነገር ግን 10 በመቶ የሚሆኑ ተጠቃሚዎች በመጨመራቸው ምክንያት የዜጎች የነፍስ ወከፍ ገቢ በ2.5 በመቶ ይጨምራል። ይህም 2.7 ቢሊዮን ዶላር (140 ቢሊዮን ብር ገደማ) ለኢኮኖሚው ይጨምርለታል።
በዚህም መንግሥት ጉድለቱን መደጎም ያዋጣዋል። የሞባይል በይነመረብ ተጠቃሚዎችን ቁጥር ማሳደግ የመሠረተ ልማት ጥያቄን መመለስ ብቻ አይደለም ያልነው ለዚህ ነው።
ወደ ነባራዊው እውነታ ስንመለስ...
በርካታ መሻሻሎች ቢኖሩም፣ ኢትዮጵያ አሁንም ከሳሃራ በታች ካሉ አገራት አንፃር እንኳን ወደኋላ ቀርታለች።
ከአራት አንዳችን ብቻ የበይነመረብ ተጠቃሚ በመሆናችን ምክንያት የዲጂታል ክፍፍሉ እየሰፋ ሲሆን የኢኮኖሚ ዕድገታችን ውሱንነት ገጥሞታል።
ከአራታችን ሦስቱ፣ በይነመረብ መጠቀም ያልቻሉት ኢትዮጵያውያን እነማን ናቸው? ለምንስ አገልግሎቱን አጡ?
በኢትዮጵያ ያለውን የዲጂታል ተጠቃሚነት ክፍተት ምን ያህል እንደሚያውቁ ለመፈተን የሚከተሉትን 5 ጥያቄዎች ሞክሩ፣
ይህንን መጠይቅ እየሞሉ ያሉት ከኢትዮጵያ ከሆነ ዕድሜዎ ከ35 በታች የመሆን ዕድሉ ሰፊ ነው። ምናልባትም ይህንን የሚያነቡት በስልክዎ ላይ ነው።
በኢትዮጵያ ስላለው የበይነመረብ ተዳራሽነት ጉዳይ ማንበብዎን አያቁሙ። ራዕያችን ለሁሉም ተዳራሽ እና በተመጣጣኝ ዋጋ የሚሽመት በይነመረብ እንዲኖር ነው።
ምንም እንኳን የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ የማሳደግ አቅሙ ከፍተኛ ቢሆንም፣ የበይነመረብ ተዳራሽነት በኢትዮጵያ ከቦታ ቦታ እና ከማኅበረሰብ ማኅበረሰብ ያልተመጣጠነ ከመሆኑም ባሻገር በጣም ውድ ነው። ብዙ ዜጎች ከበይነመረብ አገልግሎት ተጠቃሚነት ተገልለው ይገኛሉ።
የበይነመረብ አገልግሎት ከማያገኙ የማኅበረሰብ ክፍሎች መካከል ቀድሞውኑም ተጋላጭ የሆኑ የማኅበረሰብ ክፍሎች ናቸው። እነዚህም የገጠር ነዋሪዎች፣ በዕድሜ የገፉ ዜጎች፣ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው የማኅበረሰብ ክፍሎች፣ እንዲሁም ሴቶች ናቸው።
የገጠር ሰዎች በኢትዮጵያ ከከተማ ሰዎች ያነሰ የበይነመረብ ተጠቃሚዎች ናቸው። ነዋሪነታቸው ገጠርም ይሁን ከተማ፣ ስርዓተ ፆታን መሠረት ያለው የተጠቃሚነት ክፍተት እየከፋ ነው።
እ.ኤ.አ. በ2018 9 በመቶ የሚሆኑት ወንዶች የበይነመረብ ተጠቃሚ ሲሆኑ፣ ከሴቶቹ ግን 5 በመቶዎቹ ብቻ ነበሩ የሚጠቀሙት፤ የ4 በመቶ ልዩነት አለው። ከሦስት ዓመት በኋላ በ2021 ልዩነቱ 9 በመቶ ደርሷል። 20 በመቶ ወንዶቸ በይነመረብ የሚጠቀሙ ሲሆን፣ ከሴቶቹ ደግሞ 11 በመቶዎች ብቻ ናቸው። (ኢንክሉሲቭ ኢንተርኔት ኢንዴክስ፣ 2018-2021)
መጠይቁን ከላይ ከሞሉ፣ ገጠር የሚኖሩ 1 በመቶ ሴቶችና 4 በመቶ ወንዶች ብቻ በይነመረብ ተጠቅመው እንደሚያውቁ ተናግረዋል። (ዩኤስኤይድ፣ 2016)
እዚያው መጠይቅ ላይ፣ ወጣት ኢትዮጵያውያን ዕድሜያቸው ከ30 በላይ ከሆኑት የበለጠ የበይነመረብ ተጠቃሚ ናቸው። በርግጥ ከ4 በይነመረብ ከተጠቀሙ ሰዎች ውስጥ 3ቱ ወጣቶች ናቸው፤ ከ10ሩ ደግሞ 6ቱ ወንዶች ናቸው (ዩኤስኤይድ፣ 2016)
የበይነመረብ አገልግሎት የማግኘት ዕድል በትምህርት ዕድልም ይወሰናል። ከሁለተኛ ደረጃ በላይ ትምህርት የቀመሱ 65 በመቶ ወንዶች እና 41 በመቶ ሴቶች በ2008 በይነመረብ ቢያንስ አንዴ ተጠቅመዋል። (ዩኤስኤይድ፣ 2016)
በሚገርም ንፅፅር፣ ያልተማሩ ወንዶች እና ሴቶች መካከል ከ2 ሺሕ ሰዎች አንዳቸው ብቻ ናቸው በ2008 ኢንተርኔት የተጠቀሙት።
ብዙዎቹ ኢትዮጵያውያን የበይነመረብ ተጠቃሚዎች በስልካቸው ነው የሚጠቀሙት።
እ.ኤ.አ. በ2020 ከዓለም ዐቀፉ የቴሌኮሙኒኬሽን ኅብረት በሰበሰበው ዳታ፣ ከአምስት ኢትዮጵያውያን መካከል አንዳቸው ብቻ ንቁ የሞባይል የበይነመረብ ተጠቃሚ ናቸው። ከ500 ኢትዮጵያውያን መካከል የመሥመር በይነመረብ ብሮድባንድ የሚጠቀሙት አንዳቸው (አንድ ሰው) ብቻ ናቸው።
የበይነመረብ ተዳራሽነት ልዩነት በበርካታ የመሠረተ ልማት ተግዳሮቶች የተፈጠረ ነው። የመሥመር በይነመረብ አገልግሎት የኤሌክትሪክ ኃይል ይፈልጋል። ኤሌክትሪክ ኃይል የሚያገኙት ደግሞ 48.2 በመቶ የሚሆኑት ኢትዮጵያውያን ብቻ ናቸው (እንደ ዓለም ባንክ መረጃ)። ገጠር ውስጥ የሚኖሩ ቤተሰቦች ኤሌክትሪክ የማግኘት ዕድላቸው (36.3 በመቶዎቹ ብቻ) ከከተማ ነዋሪዎች አንፃር (92.8 በመቶ) ሲታይ ዝቅተኛ ነው።
በቂ የመዋዕለ ንዋይ ፍሰት አለመደረጉም የኢትዮቴሌኮምን የመሠረተ ልማት ግንባታ ውሱን እንዲሆን አድርጎታል። በተጨማሪም የተዘረጉት ኔትዎርኮች ጊዜ ያለፈባቸው በመሆናቸው አስተማማኝ እና ሰፊ አገልግሎት መስጠት አልቻሉም።
ከአስፈላጊነቱ በተቃራኒ ሰፊ ተዳራሽነት ያለው አስተማማኝና ፈጣን የሞባይል በይነመረብ አገልግሎት በጣም ውሱን ነው።
እ.ኤ.አ. በ2016 ከ10 ኢትዮጵያውይን መካከል 6ቱ ሞባይል ስልክ አላቸው (አይቲዩ፣ 2016)። የኢትዮቴሌኮም የቅርብ ጊዜ ሪፖርት እንደሚያሳየው ከሆነ ደግሞ ከ5 ኢትዮጵያውያን መካከል አንዳቸው ብቻ የሞባይል በይነመረብ ተጠቃሚ ናቸው (የኢትዮቴሌኮም ሪፖርት 2013)
97 በመቶ ኢትዮጵያውያን የሚኖሩት የ2ጂ ሞባይል ኔትዎርክ አገልግሎት ማግኘት የሚችሉበት አካባቢ ነው። ነገር ግን ኔትዎርኩ 44 በመቶ የሚሆኑ ኢትዮጵያውያንን ብቻ ነው ማስጠቀም የሚችለው።
በኢትዮጵያ ያለው የ2ጂ ኔትዎርክ በጣም የሚዘገይ ነው። አንዳንዴ በሰከንድ 67 ኪሎ ባይት ዳታ ብቻ ነው የሚያስተላልፈው። በዚህም ምክንያት ዘመናዊ ድረገጾች እና የኢሜይል ሳጥኖችን መክፈት ይቸግራል። ዩቱዩብ ማየትማ ከናካቴው አይታሰብም።
85.5 በመቶ የሚሆኑት ኢትዮጵያውያን ደግሞ 3ጂ የሞባይል ኔትዎርክ በሚገኝበት አካባቢ ይኖራሉ። ይህም 2 ሜጋ ባይት ዳታ በሰከንድ ይሠራል።
2 ሜጋ ባይት በሰከንድ ማውረድ በሚችል በይነመረብ ማኅበራዊ ሚዲያ መጠቀም እና መልዕክት መለዋወጫዎችን መጠቀም ይቻላል። መደዋወል እና ቪዲዮ መመልከት፣ ሙዚቃ ማደመጥም ይቻላል።
የ4ጂ ኔትዎርክ ለ7 በመቶ የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን ተዳራሽ ሲሆን፣ በተወሰኑ የአዲስ አበባ ክፍሎች ብቻ ይገኛል። ማዳረስ የሚችለው አቅሙ በ400 ሺሕ ሰዎች የተገደበ ነው። በአጭሩ፣ በአዲስ አበባ ከሚኖሩ 10 ሰዎች መካከል አንዳቸው ብቻ አገልግሎቱ ይደርሳቸዋል።
ነገር ግን ኢትዮጵያ፣ የኢኮኖሚ አቅሟ ያድግ ዘንድ፣ የ4ጂ በይነመረብ አቅርቦት ለበርካታ ዜጎች በብዙ ክልሎች መዳረስ አለበት።
የመሠረተ ልማቱ እና እንደ ስርዓተ ፆታ ያሉት ማኅበራዊ ተግዳሮቶቹ በቂ ያልሆኑ ይመስል፣ ፖለቲካዊ ተግዳሮቶችም አሉ።
ምንም እንኳን የበይነመረብ ተዳራሽነት ለኢኮኖሚያዊ ዕድገት፣ ለአካታችነት እና እኩልነት ለመጫወት ወሳኝ ሚና ቢኖረውም ቅሉ፣ መንግሥት - ከራሱ ግብ በተቃራኒ - የበይነመረብ ግንኙነት በማቋረጥ ሐሳብን የመግለጽ ነጻነትን ለመገደብ ይሞክራል።
በይነመረብን ማቋረጥ ዜጎች በመንግሥት ላይ ያላቸውን እምነት ከማጉደል እና የመንግሥትን ሰብዓዊ መብቶችን የማክበር ቁርጠኝነት ከመቃረኑም ባሻገር፣ የአገራችንን መልካም ገጽታ በዓለም ዐቀፍ መድረኮች የሚያጎድፍ እና በኢትዮጵያ የዲጂታል ኢኮኖሚ በ2025 ለመገንባት የወጣውን ስልታዊ ዕቅድ ያደናቅፋል።
መንግሥት የብሔራዊ ደኅንነት፣ የሕዝባዊ ስርዓት፣ የአገር ዐቀፍ ፈተናዎች ምሥጢር መጠበቅ የመሳሰሉትን ለበይነመረብ ማቋረጡ እንደ ምክንያት ሲጠቅስ ይደመጣል። ሆኖም የበይነመረብ መቆራረጡ ኢኮኖሚውን፣ የአገር ገጽታን እና ሰብዓዊ ደኅንነት ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ ነው።
ባሉፈት አምስት ዓመታት፣ ቢያንስ 17 ጊዜ የተመዘገቡ ከፊል ወይም ሙሉ የበይነመረብ መቆራረጦች ነበሩ። በዚህም ማኅበረሰቦች እርስበርሳቸው፣ ኢትዮጵያ ከመላው ዓለም ያላት ግንኙነት፣ እንዲሁም የንግድ ሥራዎች ተስተጓጉለዋል።
"ከጥቅምት 2013 ጀምሮ በይነመረብ እና ሌሎችም የመገናኛ ዘዴዎች የተቋረጡበት የትግራይ ክልል የችግሩ የመጨረሻው ገፈት ቀማሽ ነው። ሌሎችም ለጦርነቱ እና ግጭቶች ተጋላጭ የሆኑ ክልሎችም ተደጋጋሚ የበይነመረብ መቆራረጥ ሰለባ ሆነዋል። ብዙዎቹ አሁንም በቅጡ አልተመዘገቡም። በምዕራብ ኦሮሚያም እንዲሁ ተደጋጋሚ የበይነመረብ መቆራረጥ አለ።"
የኢትዮጵያ መንግሥት ሁሉንም ዓይነት የመገናኛ ዘዴዎች ወለጋ ውስጥ ካቋረጠ ከአንድ ወር በላይ ሆኖታል። ቤተሰቦች ሊገናኙ ባለመቻላቸው በበረጃ ጭለማ ውስጥ እየተጎዱ ነው። እንዴት እየሰነበቱ እንደሆነ አናውቅም፤ መገናኛ ዘዴ የለንም። ማኅበረሰባችን ውስጥ ያለው ጭንቀት ብዙ ነው፤ ቤተሰቦቻችን በሕይወት መኖራቸውን እንኳን እርግጠኛ አይደለንም።
የኢትዮጵያ መንግሥት የበይነመረብ ግንኙነቶችን በምዕራብ ኦሮሚያ እና በደቡብ ኦሮሚያ ካቋረጠ ሁለት ወራት አለፉ (ከጥር 2012 ጀምሮ)። ይህም የሞባይል በይነረመብ ግንኙነት፣ የመሥመር በይነመረብ ግንኙነት፣ የስልክ መሥመሮች፣ ወይም ሌሎች እንደ ዋትሳፕ፣ ትዊተር እና ፌስቡክ ያሉትንም ይጨምራል። በነዚህ አካባቢዎች የሚኖሩ ሰዎች ምንም ዓይነት መረጃ ስለኮሮና ቫይረስ ስርጭት እያገኙ አይደልም። የቫይረሱ ስርጭት በጣም ሊጎዳቸው ይችላል የሚል ስጋት አለኝ። እናም መንግሥት የበይነመረብ ማቋረጡን በአስቸኳይ እንዲያነሳ እጠይቃለሁ።
የመንግሥት የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስልታዊ ዕቅድ እንደሚያሳየው፣ መንግሥት ዲጂታል ቴክኖሎጂን "አካታች፣ ዕውቀትን መሠረት ያደረገ እና የበለፀገ ኅብረተሰብ" ለመፍጠር የሚያስችል እንደሆነ ያምናል።
የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ልማት ስልታዊ ዕቅድ በበይነመረብ አማካኝነት በሚገኝ ገበያ፣ ቱሪዝም፣ ምርት፣ እና አገልግሎቶች ላይ ተስፋ ይጥላል።
"በይነመረብ ለዘመናዊ ንግድ ሥራ የኅልውና መንገድ ነው። የኢትዮጵያ ጀማሪ ንግድ ሥራዎች ደግሞ በዚህ ውድድር በበዛበት ከባቢ ውስጥ ከሁሉም የበለጠ ጠንክረው መሥራት አለባቸው። ምክንያቱም ገበያው አልዳበረም፤ ሆኖም የበይነመረብ መቆራረጥ ሥራቸውን ከማስተጓጎሉም በተጨማሪ ከናካቴው ከስረው እንዲዘጉ ሊያደርጋቸው ይችላል። በዚህ ጊዜ ለቴክኖሎጂ ጅምር ንግድ ሥራዎች ፣ በይነመረብ ማለት "ሱቃቸው" ማለት ነው፤ የገበያ ቦታቸው ነው። ያለእርሱ ምንም መሥራት አይችሉም። ንግዶች ሲስተጓገሉ ደግሞ አገሪቷም ብዙ ታጎድላለች።"
የኢትዮጵያ መንግሥት በይነመረብን አገር ዐቀፍ የኢኮኖሚ ዕድገት ለማነቃቃት ሊጠቀምበት ካቀደ፣ ዜጎች በይነመረብን ሊጠቀሙበት የሚችሉበትን ሁኔታም ማክበር እና በነጻነት መኖር፣ መማር፣ መሥራት እና መገናኘት እንዲችሉ ማድረግ አለበት።
ይህ ሥልጣን ላይ ያሉትን ሰዎች ስጋት ላይ ይጥል ይሆናል፣ ነገር ግን መንግሥት ራሱ በዲጂታል ኢትዮጵያ ዕቅዱ ተናግሮታል፤
"የዲጂታል ዕድሎችን መጠቀም አዲስ አመለካከትን እና የአመራር ዘዴን ከመንግሥት ይጠብቃል። ፈጠራን ማስቻል ማለት የማያውቁትን ነገር በፀጋ መቀበል ነው።"
እኛም ካርዶች በዚህ አባባል እንሥማማለን።
ግለሰብ ከሆኑ፣ ድርጅትም ይሁን ኩባንያ ቢወክሉ፣ ከእኛ ጋር ተመሳሳይ አቋም ካልዎት፣ እባክዎ ይህንን የአድቮኬሲ ትርክት #KeepItOn ከሚል ሐሽ ታግ ጋር ለወዳጆችዎ ያጋሩ። ሰብዓዊ መብቶችዎ እንዲከበሩ ድምፅ አውጥተው ይናገሩ።
ይህ ተረክ የተዘጋጀላችሁ በካርድ እና ዳታ ፎር ቼንጅ በተባለ ድርጅት ትብብር በስሞል ሚዲያ እና ኦሚድያር ኔትዎርክ በሚደገፈው የዳታ ፎር ቼንጅ የዳታ ተረኮች ፕሮግራም ነው።
ምስጋና፤ ከፍተኛ የዳታ ተመራማሪዋ ኤቭሊና ጁዴካይት፣ የዳታ ተባባሪ ተመራማሪዋ አሊስ ፌንግ፣ የግራፊክ ዲዛይነሯ ሱራቲ ፑሪ፣ ጋዜጠኛ ዳንኤላ ኪው ሌፒዝ